በማዕድንና ነዳጅ ሚ/ር የማዕድን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በክብርት ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የተመራ የልዑካን ቡድን በምዕራብ አፍሪካዊት ሀገር ማሊ የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት አደረገ

ጉብኝት ያዘጋጀው ‘Allied Gold Cop’ የተባለ የማዕድን ልማት ኩባንያ ሲሆን ኩባንያው በቤንሻንጉል-ጉምዝ፣ አሶሳ ዞን፣ ኩርሙክ ወረዳ ዲሽ እና አሻሽሬ በተባሉ ቦታዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ሊለሙ የሚችሉ ሁለት (2) የወርቅ ክምችት ምርመራ በማድረግ በቅርቡ ወደ ልማት ለመሸጋገር የምርት ፈቃድ ለመውሰድ የተዘጋጀ ኩባንያ ነው፡፡
ሰባት አባላትን የያዘው የልዑካን ቡድኑ የተውጣጣው ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር፣ ከክልሉ ማዕድን ልማት ኤጀንሲ፣ ከክልሉ ከአካባቢና ማህበረሰብ ጥበቃ ልማት ቢሮ እና ከአሶሳ ዞን ኩርሙክ ወረዳ ነው፡፡
ልዑካን ቡድኑ በማሊ፣ ካይስ ሪጅን፣ ሳዲዮላ በተባለ ቦታ ላይ የሚያካሄደውን የወርቅ ማምረቻ ቦታ ለመጎብኘትና በዋናነት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ስለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ የመሰረተ-ልማት ዝርጋታ እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በኩባንያውና በማህበረሰቡ መካከል ያለውን ልምድና ተሞክሮ በመቀመር ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡
የልኡካን ቡድኑ ማሊ-ባማኮ ‘Senov International Airport’ በማዕድን ሚኒስትሩ የተከበሩ M.Boubou Cisse፣ በባለማዕረግ ወታደራዊ ሃላፊዎችና በከተማ ከንቲባ አቀባበል እና ሽኝት ተደርጎለታል፡፡
ሳዲዮላ የወርቅ ማምረቻ ከዋና ከተማ ባማኮ በደቡብ ምዕራብ በኩል 700 ኪ.ሜ ላይ የሚገኝ ሲሆን እ.ኤ.አ ከ1994 ጀምሮ በማምረት ሂደት ላይ እንደሚገኝና በተጓዳኝ የወርቅ ፍለጋ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡
የልዑካን ቡድን ወደ ወርቅ ማምረቻ ቦታው እንደደረሰ የእንኳን ደህና መጣችሁ እና ታሪካዊ የፍለጋና የምርት ሂደት ገለፃ በማድረግ የመስክ ጉብኝት በማዕድን ማውጫ፣ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ፣ የጥናት ቦታ፣ እንዲሁም ኩባንያው ያስገነባው የጤና ተቋም ጉብኝት ተካሂዷል፡፡ ኩባንያው ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት እና በማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ዙሪያ ውይይት የተደረገ ሲሆን በመንገድ ዝርጋታ፣ በመጠጥ እና የመስኖ ውሃ ልማት፣ የት/ቤቶች ግንባታ እንዲሁም በኩባንያው ዙሪያ ለሚገኙ አስራ ሰባት (17) ቀበሌዎች የህክምና አገልግሎት በመስጠት ለማህበረሰቡ ማህበራዊ ግዴታውን እየተወጣ የሚገኝ ኩባንያ መሆኑን ለቅ ተችሏል፡፡
የማዕድን ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ስመኝ ውቤ በጉብኝቱ ወቅት ለተገኙ የውጭ ሚዲያዎች ስለጉብኝቱ ዓላማ፣ ስለ ሀገራችን የማዕድንና ነዳጅ ሀብት እንዲሁም ልዑካኑ ከጉብኝቱ የቀሰመው ተሞክሮ እና ወደፊት ከኩባንያው ጋር በጋራ ሊተገበሩ የሚገባቸውን ነጥቦች አስረድተዋል፡፡
ልዑኩ በተለይም ከክልሉ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርከኖች የተውጣጡ አመራሮች በዘመናዊ መንገድ የወርቅ አመራረት፣ የማህበረሰብ ተጠቃሚነት እና የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ልምድና ተሞክሮ የቀሰሙ ሲሆን Allied Gold Cop ኩባንያም በቅርቡ በአሶሳ ዞን ኩርሙክ ወረዳ ለሚገነባው የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ ከፍተኛ እገዛ ለማድረግና በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በማህበረሰብ ልማት፣ በመሰረተ-ልማት ዝርጋታና እና ከልዩ ልዩ ገቢዎች መንግስትንና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

Leave A Comment

MoM