ኢ/ር ታከለ ኡማ በአፋር ክልል የሚገኙ የማአድን ልማት ስራዎችን እየተመለከቱ ነው

ኢ/ር ታከለ ከአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ጋር በመሆን የፖታሽ፣ ጨውና ብሮሚን ምርቶች ላይ እየተከናወኑ ያሉ የማአድን ልማቶችን ተመልክተዋል።
ኢ/ር ታከለ አፍዴራ አካባቢ “ታናራሙ ኬሚካልስ” በተባለ የቻይና ኩባንያ እየተገባ የሚገኘው የብሮሚን ፋብሪካ የጎበኙ ሲሆን ፋብሪካው በ57 ሚሊየን ዶላር ወጪ እየተገነባ የሚገኝ ነው።
ፋብሪካው “ሀይድሮጅን ብሮማይድ አሲድ” አዘጋጅቶ ለውጪ ገበያ የሚያቀርብ ይሆናል።
ፋብሪካው በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ስራ የሚገባ ይሆናል።
ፋብሪካው በአመት 40 ሺህ ቶን የማምረት እቅድ ያለው ሲሆን ምርቱን ለውጪ ገበያ በማቅረብ በአመት 12 ሚሊየን ዶላር የማግኘት እቅድ ይዟል።
የፋብሪካው ሀላፊዎች ለግንባታ የሚያስፈልጓቸው ግብአቶች ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላ የመዘግየት ችግር እያጋጠማቸው መሆኑና እንዲፈታላቸው ለኢ/ር ታከለ ጥያቄ አቅርበዋል።
ፋብሪካው የገጠመውን የግብአት አቅርቦት መጓተት በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንዲፈታላቸው እንደሚያደርጉና ኃላፊዎቹም ፋብሪካው በፍጥነት ወደ ምርት እንዲገባ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ኢ/ር ታከለ ኡማ ከአቶ አወል አርባ ጋር በመሆን የአፍዴራ የጨው ማውጫን ጎብኝተዋል።
ከጨው ማምረት ሂደቱ ጋር የሚነሱ የፍትሀዊነት ጥያቄዎች የሚነሱ ሲሆን እነዚህ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ኢ/ር ታከለ ገልፀዋል።
ጨው የማውጣት የመጀመሪያዎቹ ሂደቶች በሰው ሀይል ሊሰሩ የሚችሉ በመሆናቸው ለአካባቢው ማህበረሰብ ክፍት መሆን እንዳለባቸው የተናገሩት ኢ/ር ታከለ ፋብሪካዎች ከፍተኛ ፋይናንስ የሚጠይቀው እሴት የመጨመር ተግባር ላይ ብቻ እንዲሰማሩ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ይህ በፍጥነት ተግባር ላይ እንዲውልም ከክልሉ ጋር በጋራ እንደሚሰራ ኢ/ር ታከለ ተናግረዋል።

Leave A Comment

MoM