የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ::

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለማካሄድ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚያዚያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል በተካሄደው መርሃግብር ላይ ተፈራርመዋል።
የመግባቢያ ሰነዱ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዘመናዊ የምርቶች ግብይት ሥርዓት፣ በግብይት ሰንሰለት ቅንጅት፣ በኤሌክትሮኒክ ግብይት ጥራትና በመጋዘን ኦፐሬሽን ያካበተውን ሰፊ ልምድ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የሀገራችንን የማዕድን ዘርፍ በመምራት ካለው ጥልቅ ተሞክሮ ጋር በማጣመር በኢትዮጵያ ዘመናዊ የማዕድናት ግብይት ማእከል እና ስርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ይህም በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶችና ኢትዮጵያዊያን አምራቾች ግልጽ የሆነ አሠራርን በመዘርጋት እኩል ተጠቃሚነትን ያሰፍናል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በመግባቢያ ሰነዱ መሰረት በጋራ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ለተለያዩ የኢትዮጵያ ማዕድናት (ለምሳሌ እንደ ኦፓል፣ ኢመራልድ፣ ሳፋየር፣ ታንታለም፣ ሊቲየም፣ ፖታሽ፣ ብረትና ለመሳሰሉት) በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት(ተፈላጊነት) ያላው የምርት ደረጃ ውሎችን ማዘጋጀትና ለብሔራዊ የማዕድን ግብይት የሁለቱንም ተቋማት የሰው ኃይል፣ ላቦራቶሪዎችና ተቋማዊ አቅም በመጠቀም፤ የግብይት አሠራሮችን፣ ሞዴሎችን፣ የሥራ ሂደቶችን፣ ደንብና መመሪያዎችን መቅረጽ ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የማዕድናት ግብይትን ማካሄድና በአገር አቀፍ ደረጃ የሁሉም የግብይት ተዋንያንን ተሳትፎ የማረጋገጥ፤ በምርት ገበያው የሚከናወኑትን የማዕድን ግብይት በቀላሉ ለመቆጣጠር እንዲቻል የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርን የቁጥጥር ማዕቀፍ የመከለስ፤ የሚከናወነውን የማዕድን ግብይትም ዲጂታላይዝ የማድረግና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት መድረክን በመጠቀም የኢትዮጵያ ማዕድናት እንደ ምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ነጻ ገበያ የመሳሰሉ ገበያዎች ላይ በቀላሉ እንዲገቡ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡
በማዕድን ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተጠቃሚዎችን በጥራት ደረጃ አጠባበቅና ስለዓለም አቀፍ ግብይት ደረጃ አቅማቸውን ለመገንባት ስልጠና መስጠትና የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የማዕድናት ዋጋና ሌሎችንም መረጃዎች መሰብሰብ፣ መተንተንና ለተጠቃሚዎች ማሰራጨት የመሳሰሉት ተግባራት ተካቷል።

Leave A Comment

MoM