63 የማአድን ተቋማት ፈቃድ ተሰረዘ፡፡

የማአድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ኢ/ር ታከለ ኡማ ፈቃዳቸው በተሰረዘው ተቋማትና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የማድን ፈቃድ አውጥተው በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ ያላዋሉ ተቋማት ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እርምጃ መውሰዱንም ኢ/ር ታከለ ገልጸዋል፡፡

በተገቢው ወቅት የተሰጣቸውን ፈቃድ ያለማደስ፣ በውል የገቡትን ግዴታ ባለማክበር፣ከአቅም በታች በማምረት  እንዲሁም የሮያሊቲ ክፍያ ባለመፈጸም ምክንያት የተሰጣቸው ፈቃድ እንዲሰረዝ ምክንያት ሆኗል፡፡

ፈቃዳቸው ከተቋረጠው 63 ተቋማት ውስጥ 38 ተቋማት በማአድን ምርት ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሲሆን ቀሪዎቹ 25 ተቋማት ደግሞ በማአድን ምርምር ላይ ተሰማርተው የነበሩ ናቸው፡፡

ኢ/ር ታከለ ኡማ በመግለጫቸው አያይዘውም በማአድን ዘርፉ ያሉ የተለያዩ መረጃዎች የተደራጁበት እንዲሁም ፈቃድ የመውሰድና የማመልከት ሂደቱን የሚያቀልና ዘመናዊ የሚያደርግ የካዳስተር ፖርታል ስርአት በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ካዳስተር ፖርታሉ በኢንተርኔት የማአድን ማምረትና የምርምር ፈቃድ ማውጣት የሚቻልበት እንዲሁም የማአድን ሀብት የኢንቨስትመንት መረጃዎች የተካተቱበት ነው፡፡

የካዳስተር ፖርታል ስርአቱ ዘርፉን በቴክኖሎጂ የሚደግፍና ግልጸኝነትን በማስፈን በኩል ሚናው የጎላ እንደሚሆንም ኢ/ር ታከለ ኡማ ተናግረዋል፡፡

ኢ/ር ታከለ ኡማ ባለፉት አምስት ወራትም ከማዕድን ዘርፍ 302.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።ከማአድን ምርት የሚገኘው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝ ያሳወቁት ኢ/ር ታከለ ኡማ  ለዚህም የኮንትሮባንድ ንግድን  ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በተሰራው የቅንጅት ስራ እንዲሁም የማአድን ምርት ማነቆ የሆኑ የመሰረተልማትና የአቅርቦት ችግሮችን መፍታት መቻሉ ለምርቱና ገቢ መጨመር ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የማአድንና ነዳጅ ዘርፉን ለማሳደግና በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ለመደገፍ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ፈቃዳቸው የተነጠቀባቸው የማአድን ቦታዎች በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲገቡና የሐገርና የህዝብ ሀብቶች የሆኑት የማአድን ሀብቶቹ  በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረግ ይሆናል፡፡

Leave A Comment

MoM