
“ ከዛሬ ጀምሮ ነዳጅ የሚጠቀሙ ማንኛውም ትልልቅ መኪኖች (ትራክ) ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት የተከለከለ ነው “ – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
በሶማሌ ክልል ካሉብ በአመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርቃቱ ወቅት ባሰሙት ዘለግ ያለ ንግግር ፕሮጀክቱ ለሃይል ማመንጫ እና ለክሪፕቶ ማይኒንግ ሥራዎች አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን ጭምር የሚያቀርብ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ ቢበዛ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ 2 ሺ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ከተማ እና ወደ ክልል የሚሄዱ ባሶች አሁን ከሚጠቀሙት ነዳጅ ወደ ጋዝ እንቀይራለን “ ሲሉ የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም የትራንስፖርት ወጪ በ 50 በመቶ የሚቀንስ መሆኑን አስረድተዋል።

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምርቃቱ ወቅት ባሰሙት ንግግር ምን አሉ?
“ በእዚህ አመት ቢበዛ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ 2 ሺህ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ከተማ እና ወደ ክልል የሚሄዱ ባሶች አሁን ከሚጠቀሙት ነዳጅ ወደ ጋዝ እንቀይራለን።
እነዚህ 2 ሺህ መኪኖች ሲቀየሩ የትራንስፖርት ዋጋ ቢበዛ ወይም ቢያንስ አሁን ካለው በ 50 በመቶ በሚቀጥለው አመት እንቀንሳለን።
በከተሞቻችን ያለው ዋናው ችግር የ ሊቪንግ ኮስት ችግር ነው የሊቪንግ ኮስት አንደኛው ምክንያት ቤት ነው።
ከ1.5 ሚሊየን በላይ ቤቶችን እንገነባለን ያልነው የዜጎቻችን የሊቪንግ ኮስት ጫና የሚያስከትለውን አንዱን ችግር እንቀርፋለን ለማለት ነው።

ሁለተኛው ትራንስፖርት ነው በከተማ ትራንስፖርት 50 በመቶ አሁን ያለውን ኮስት ቀነስን ማለት በአነስተኛ ገቢ ወጥተው የሚገቡ ሰርተው የሚውሉ ዜጎች በእጅጉ ኑሯቸውን ለማገዝ የሚጠቅም ነው።
ሦስተኛ ኢነርጂ ስናመርት ለክሪፕቶ ብቻ ሳይሆን ለብርሃንም ጭምር ስለሆነ ጋዝ ምግባችን፣ ጋዝ ትራንስፖርታችን፣ ጋዝ ለኢነርጂ ማምረቻ የሚውል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው።
ትላልቅ መኪና ወይም ትራክ ወደ ኢትዮጵያ ስታስገቡ የነበራቹ ዜጎች ከዛሬ ጀምሮ ልክ ለትናንሽ መኪኖች ከኤሌክትሪክ መኪና ውጪ ማስገበት ታግዶ እንደቆየው ከዛሬ ጀምሮ ነዳጅ የሚጠቀሙ ማንኛውም ትራክ ወደ ኢትዮጵያ መስገባት የተከለከለ ነው።
በአንጻሩ ማንኛውም የግል ባለሃብት ጋዝ የሚጠቀሙ ትራኮች የሚያስገባ ከሆነ ከቀረጥ ነጻን(Duty free) ጨምሮ አስተማማኝ ድጋፍ የሚደረግላቹ ሲሆን እንደሃገር እያወጣን ያለነውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ ፣ የሎጅስቲክስ ኮስት ለመቀነስ፣ ትራንስፖርት ለማሳለጥ የግሉ ሴክተር ከእዚህ ቀን በኋላ በጋዝ የሚጠቀሙ ትራኮች በማስገባት የሃገሩን የኢኮኖሚ እድገት እንዲያፋጥን ከአደራ ጭምር ላሳስብ እወዳለሁ “ ብለዋል።
ትዊተር፦ https://twitter.com/MinistryofMine_
ድረ ገጽ፦ www.mom.gov.et
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/MinesandPetroleum/
Telegram: – https://t.me/+-aNetmkG-WY2YWM8
Email: info@mom.gov.et